Top Banner
Site Map Links Contact Us
Home
Election Day Countdown
About NEBE
What's New
Electoral System
Legal Framework
Electoral Operations
Maps & Data
Domestic & International Observers
Election Results
Photo Gallery
 
   
 

የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በምርጫ ጣቢያዋች ሊከተሏቸው የሚገቡ የአሰራር ደንቦች

መገናኛ ብዙሃን የምርጫውን ሂደት ተከታትሎ በመዘገብ መራጩ ሕዝብ ስለሂደቱ የተሟላ ግንዛቤ እንዲኖረው በማስቻል ረገድ ጉልህ ሚና ይጫወታሉ፡፡

በማናቸውም የኤሌክትሮኒክስ ወይም ሕትመት ሚዲያ የሚሰሩ የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ ጋዜጠኞች በየትኛውም የምርጫ ጣቢያና የምርጫ ክልል ጽሕፈት ቤት ተዘዋውረው የምርጫውን ሂደት ለመዘገብ የሚያስችላቸውን የፕሬስ ዕውቅና ፈቃድ ከቦርዱ የፕሬስና ኢንፎርሜሽን ክፍል ማግኘት ይኖርባቸዋል፡፡  ይህንኑ የእውቅና ፈቃድ ለማግኘት ከማስታወቂያ ሚስቴር ጋዜጠኛ መሆናቸውን የሚገልፅ መታወቂያ ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል፡፡

ጋዜጠኞች በየትኛውም የምርጫ ጣቢያም ሆነ የምርጫ ክልል ጽሕፈት ቤት በሚገኙበት ጊዜ ይህንኑ ከቦርዱ የተሰጣቸውን የጋዜጠኞች መታወቂያ ካርድ ማንጠልጠል ይኖርባቸዋል፡፡

የሚዲያ ተወካዮች በምርጫ ሂደት ዘገባዎቻቸው በሚከተሉት መሠረታዊ የጋዜጤኝነት መርሆዎች ይዘግባሉ፡፡

መረጃ በሚሰበሰቡበትና በሚያሰራጩበት ወቅት ዘገባዎቻቸው ትክክለኛ፣ ሚዛናዊና ከግል ስሜት ነፃ እንዲሆኑ ይጥራሉ፡፡

በዘገባዎቻቸው ተዓማኒነት እና ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸውን የዜና ምንጮች ይጠቀማሉ፡፡

ወሳኝ የሆኑ መረጃዎችን አይደብቁም፤ ሆን ብለውም አያዛቡም፡፡

ዜናዎችን፣ መረጃዎችንና ምስሎችን በሚያሰባስቡበት ወቅት ማንነታቸውን አይደብቁም፤

በማናቸውም የዜናም ሆነ የዘገባ ሥራዎቻቸው በዘር፣ በሃይማኖት፣ በፆታ፣ በቋንቋ፣ በፖለቲካ አመለካከት ወይም ማሕበራዊ ደረጃ ልዩነት አያደርጉም፡፡

የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በምርጫ ጣቢያዎችና ምርጫ ክልል ጽሕፈት ቤቶች የሚከተሉት መብቶች አሏቸው፡፡

የድምፅ አሰጣጡን ሂደት የሚያደናቅፍ እንቅስቃሴ እስካላደረጉ ድረስ የምርጫ ጣቢያው ከሚከፈትበት ከጧቱ 12 ሰዓት ጀምሮ እስከሚዘጋበት ከምሽቱ 12 ሰዓት ድረስ በጣቢያው የመገኘት፣ የቆጠራውን ሂደትና የውጤት አገላለፅ ሥርዓቱን የመከታተል መብት አላቸው፡፡

የምርጫ አስፈፃሚዎችን ሥራ በማያውክ መልኩ በምርጫ ጣቢያው ውስጥ የመዘዋወር መብት አላቸው፡፡

መራጮችን፣ የዕጩ ተወዳዳሪዎች ወኪሎችን ታዛቢዎችንና የምርጫ አስፈፃሚዎችን የመጠየቅና መረጃ የማግኘት መብት አላቸው፡፡  ይህን ለማድረግ ግን መራጮች፣ የዕጩ ተወዳዳሪ ወኪሎችና ታዛቢዎች ፈቃደኛ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡  የምርጫ አስፈፃሚዎች ከሥራቸው ፋታ በሚያገኙበት ሰዓት ቃለ ምልልሱን ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡  ማናቸውም ቃለ ምልልሶች ከምርጫ ጣቢያው ውጭ መከናወን ይኖርበታል፡፡

ከምርጫው ቀን ቀደም ብሎ በምርጫ ጣቢያው የተደረጉ ዝግጅቶችን የመመልከትና ምን ያህሉ የምርጫ ቁሳቁሶች ጥቅም ላይ እንደዋሉ ጠይቆ የመረዳት መብት አላቸው፡፡  የምርጫ ውጤት ከምርጫ ጣቢያ ወደ ምርጫ ክልል ጽሕፈት ቤት በሚጓጓዝበት ወቅት አብረው ለመሄድ ይችላሉ፡፡

በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ የምርጫ ጣቢያዎችን የመጎብኘትና የመዘገብ መብት አላቸው፡፡

የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች የሚከተሉትን ሊያደርጉ አይችሉም

መራጮች ድምፅ በመስጠት ላይ እያሉ የምርጫ አስፈፃሚዎችም የመራጮችን ማንነት የማጣራት ሥራ ላይ እያሉ ቃለመጠይቅ ማድረግ አይችሉም፡፡

መራጮችንም ሆነ የምርጫ አስፈፃሚዎችን ያለፈቃዳቸው ፎቶግራፍ ማንሳትም ሆነ ቪዲዮ መቅረፅ አይችሉም፡፡

መራጮች በምስጢር ድምፅ መስጫ ውስጥ በድምፅ መስጫ ወረቀታቸው ላይ ምልክት ሲያደርጉ በምንም ሁኔታ ፎቶግራፍ ሊነሱም ሆነ በፊልም ሊቀረፁ አይችሉም፡፡  የድምፅ መስጫ ወረቀቱን አጥፊው ኮሮጆው ውስጥ በሚያስገቡበት ጊዜ ግን ፈቃደኛ ከሆኑ ምስላቸውን መውሰድ ይቻላል፡፡

የመራጮችን መዝገብም ሆነ የድምፅ ሰጪ መታወቂያ ካርዶችን የግለሰቦችን የግል መረጃዎች በሚያጋልጥ መልኩ በቅርበት በፊልም መቅረፅም ሆነ ፎቶግራፍ ማንሳት አይቻልም፡፡

መራጮች ለየትኛው ዕጩ ተወዳዳሪ ድምፃቸውን እንደሰጡ ሊጠየቁ አይገባም፡፡

የሚዲያ ቃለ ምልልሶች

ዜጠኞች ማናቸውንም ቃለ ምልልሶች ከምርጫ ጣቢያው ውጭ ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡  በቃለ ምልልሱ ወቅት የምርጫ ጣቢያ ኃላፊዎች ከሚኖርባቸው የሥራ ጫናና የጊዜ ዕጥረት አንፃር በአጠቃላይ መረጃ ነክ ለሆኑ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣሉ፡፡  ትንታኔንና የግል አስተያየትን ለሚጠይቁ ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት አይገደዱም፡፡

የምርጫ ጣቢያ ኃላፊዎች ለሚከተሉት መረጃ ነክ ጥያቄዎች መልስ ሊሰጡ ይችላሉ፡፡

የድምፅ አሰጣጡ ሂደት (የምርጫ ጣቢያው የሚከፈትበት ሰዓት፣ የመራጮች ማንነት ማጣራት፣ የቆጠራና የፀጥታ ጉዳዮችን በተመለከተ)

የተመዘገቡና እስከዛ ሰዓት ድምፅ የሰጡ መራጮች ቁጥር

የምርጫ አስፈፃሚዎች (የአምስቱ) ተግባርና ኃላፊነት፣ የወሰዷቸው ስልጠናዎች

በእስካሁኑ የምርጫ ሂደት ያጋጠሙ ችግሮች ካሉ

የምርጫ ጣቢያ ኃላፊዎች ትንታኔን ወይም የግል አስተያየትን ለሚጠይቁ ለሚከተሉት ዓይነት ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት አይገደዱም፡፡

በምርጫ ጣቢያው ባለው ውጤት መሠረት በምርጫ ክልል ወይም በአገር አቀፍ ደረጃ ስለሚኖረው ጠቅላላ ውጤት መተንበይን

በዕጩ ተወዳዳሪዎች ማንነት ወይም በፖለቲካ ፓርቲዎች ዙሪያ አስተያየት መስጠትን

በአንዱ ወይም በሌላ መልኩ አንዱን ፓርቲ ከፍ ሌላውን ዝቅ የሚያደርጉ አስተያየቶችን መሰንዘርን

ተጨባጭነት በሌላቸው ወሬዎች ተንተርሶ አስተያየት መስጠትን

 

 
     
     
       
         
             
 
 
This site is designed by Afrolink Studio
Copyright © 2005 National Electoral Board of Ethiopia. All rights reserved.