Top Banner
Site Map Links Contact Us
Home
Election Day Countdown
About NEBE
What's New
Electoral System
Legal Framework
Electoral Operations
Maps & Data
Domestic & International Observers
Election Results
Photo Gallery
 
   
 

ግንቦት 8 ቀን 1997 ዓ.ም.

የቦርዱ ሰብሳቢ ለመራጮችና የምርጫ አስፈፃሚዎች ምስጋናቸውን ገለፁ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ከማል በድሪ በትናንትናው ዕለት በተካሄደው ምርጫ መራጩ ሕዝብ ላሳየው ጨዋነትና ትዕግስት እንዲሁም የምርጫ አስፈፃሚዎች ላደረጉት ከፍተኛ ርብርብ ምስጋናቸውን ገልፀዋል፡፡

አቶ ከማል እንዳሉት እስከአሁን ለቦርዱ በደረሱ ሪፖርቶች መሠረት በትናንትናው ዕለት የተካሄደው ምርጫ በመላ ሀገሪቱ ፍፁም ሰላማዊና በተረጋጋ ሁኔታ ተከናውኗል፡፡

በዚህ ዓመት ምርጫ የመራጮች ብዛት ከ 90 በላይ ይሆናል ተብሎ እንደሚገመትና ይህም በተለይም በአዲስ አበባ የድምፅ አሰጣጡ እንዲጓተት አድርጎታል ያሉት ሰብሳቢው በተለይ በኮተቤና አየር ጤና በተባሉት አካባቢዎች መራጩ ሕዝብ እስከ እኩለ ሌሊት በመቆየት ድምፅ መስጠቱ የሚደነቅ ነው ብለዋል፡፡

ለተፈጠረው የድምፅ አሰጣጥ መጓተት ቦርዱ ይቅርታ ይጠይቃል ብለዋል፡፡  መራጮች በድምፅ አሰጣጡ መጓተት ምክንያት የደረሰባቸውን እንግልት ተቋቁመው የመምረጥ መብታቸውን መጠቀማቸው ዲሞክራሲ በኢትዮጵያ ሥር እየሰደደ መምጣቱን አመላካች ነው ብለዋል፡፡

የቦርዱ ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ተስፋዬ መንገሻ በበኩላቸው በጋሞጎፋ ዞን ሁለት የምርጫ ጣቢያዎችና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሽናሻ ልዩ የምርጫ ጣቢያ የተሳሳቱ የድምፅ መስጫ ወረቀቶች በመላካቸው ምርጫው ሳይካሄድ ቀርቷል ብለዋል፡፡  ለነዚሁ ጣቢያዎች ትክክለኛው የድምፅ መስጫ ወረቀቶች በመጪዎቹ ሦስት ቀናት እንደሚላክና መራጮች ድምፅ እንደሚሰጡ ገልፀዋል፡፡

በተመሳሳይም በጅማና አለማያ ዩኒቨርስቲዎች በተቋቋሙ የምርጫ ጣቢያዎች ለጥቂት መራጭ ተማሪዎች የድምፅ መስጫ ወረቀት አለመላኩንና ይህም በቀጣዮቹ ሦስት ቀናት ተልኮ ተማሪዎቹ ድምፅ እንደሚሰጡ አስታውቀዋል፡፡

የውጤት አገላለፅን በተመለከተ የቦርዱ ሰብሳቢ አቶ ከማል እንዳስረዱት በዛሬው ዕለት በምርጫ ጣቢያ ደረጃ ያለው ውጤት ለሕዝብ ይፋ ይሆናል፡፡  የየምርጫ ጣቢያው ውጤት በምርጫ ክልል ደረጃ ከተደመረ በኋላ ከየምርጫ ክልሉ አብዛኛውን ድምፅ ያገኙት ዕጩዎች ለየተወዳደሩባቸው ምክር ቤቶች የሚያልፉ ይሆናሉ፡፡

በድምፅ አሰጣጥም ሆነ በቆጠራው ሂደት ቅር የተሰኘ ማንኛውም ወገን አቤቱታውን ለምርጫ ጣቢያና ለምርጫ ክልል ጽሕፈት ቤት ማቅረብ እንደሚችል በዚህም ቅር ከተሰኘ ወደ ቦርዱና ሥልጣን ወዳለው ፍርድ ቤት ማቅረብ እንደሚችል ገልፀዋል፡፡

የቦርዱ ጽሕፈት ቤት እስከ ግንቦት 13 ቀን 1997 ዓ.ም. ድረስ ጊዜያዊ ውጤቶችን በምርጫ ክልል ደረጃ የሚያሳውቅ ሲሆን የቦርዱ ሰብሳቢ ሰኔ 1 ቀን 1997 ዓ.ም. በአገር አቀፍ ደረጃ ያለውን ውጤት ለሕዝቡ ይፋ ያደርጋሉ፡፡

ለበለጠ መረጃ ፕሬስ ኦፊሰር - ጌታሁን አሞኝ 09643736

ረዳት ፕሬስ ኦፊሰር ሕይወት አለማየሁ 09487576

 
     
     
       
           
           
 
 
This site is designed by Afrolink Studio
Copyright © 2005 National Electoral Board of Ethiopia. All rights reserved.