Top Banner
Site Map Links Contact Us
Home
Election Day Countdown
About NEBE
What's New
Electoral System
Legal Framework
Electoral Operations
Maps & Data
Domestic & International Observers
Election Results
Photo Gallery
 
   
 

ግንቦት 22 ቀን 1997 ..

ለቦርዱ የቀረቡ አቤቱታዎች በጥምር ኮሚቴዎች ሊጣሩ ነው

ግንቦት 22 ቀን 1997 .. በተደረገው የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ መድረክ መደበኛ ስብሰባ ላይ በኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ አነሳሽነት ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከውጭ ታዛቢዎች እና ከቦርዱ ተወካዮች የተውጣጡ ጥምር ኮሚቴዎች በአፋጣኝ እንዲዋቀሩና ለቦርዱ የቀረቡትን አቤቱታዎች እንዲያጣሩ ስምምነት ላይ ተደረሰ፡፡

አብዛኞቹ የቀረቡት አቤቱታዎች ግልፅነት የሚጎድላቸውና በማስረጃ ያልተደረገፉ ናቸውሲሉ አቶ ከማል በድሪ የብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ሊቀመንበር ገልፀዋል፡፡  ቦርዱ በመጀመሪያ የቀረቡለትን አቤቱታዎች ያጤናል፡፡  ከዚያም ችግሮችን ለይቶ አውጥቶ መጣራት የሚያሰፈልገውን ክስ ለሚዋቀሩ አጣሪ ኮሚቴዎች ያስታውቃልበማለት አብራርተዋል፡፡

ቦርዱ እስከሚመጣው አርብ ግንቦት 26 ቀን 1997 .. ድረስ ሁሉም አቤቱታ ያቀረቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ማስረጃቸውን እንዲያቀርቡ ጠይቋል፡፡

አጣሪ ኮሚቴዎች ለቦርዱ በምርመራ ያገኙትን ውጤት ሲያቀርቡ ቦርዱ የመጨረሻውን ውሳኔ እንደሚሰጥ አቶ ከማል ተናግረዋል፡፡

በምርጫ ሕጉ አንቀጽ 52 (2) መሠረት ቦርዱ ማንኛውም አዋጁን የሚጥስ ተግባር በስፋቱና በዓይነቱ የምርጫውን ውጤት እንደሚወስን በራሱ ክትትል ወይም ከተወዳዳሪዎች ወይም ተወዳዳሪዎችን ካቀረበ ፓርቲ በቂ መረጃ ካገኘ የምርጫውን ሂደት ለማቆም ወይም የምርጫውን ውጤት ውድቅ ለማድረግና እንደገና ምርጫ እንዲካሄድ ለማዘዝ ይችላል፡፡  ይህንን መሠረት አድርጎ ቦርዱ ውሳኔዎችን እንደሚያሳልፍ ተገልጿል፡፡

በአጣሪ ኮሚቴዎች የቀረቡትን የምርመራ ውጤቶች ቦርዱ ካየ በኋላ ጊዜያዊ የምርጫ ውጤቱን ሊያፀናው ወይንም ዳግም ምርጫ እንዲካሄድ ሊወስን ይችላል፡፡

ድጋሚ ምርጫ እንዲደረግ የሚወሰነው የተከሰቱት ችግሮች በተጠቀሱት የምርጫ ክልሎች ውጤት ላይ ወሳኝነት ካላቸው ብቻ እንደሚሆን የቦርዱ ሰብሳቢ አመልክተዋል፡፡

አንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በጋራ መድረኩ ውይይት ላይ ሰኔ 1 ቀን 1997 .. ቦርዱ ይፋ ሊያደርግ ያቀደውን የምርጫ ውጤት እንዲያራዝም ጠይቀዋል፡፡  በተጨማሪም የምርጫ ቦርድ ጽሕፈት ቤት እያስታወቀ ያለው የጊዜያዊ የምርጫ ውጤት እንዳይቀጥል ጠይቀዋል፡፡

አቶ ከማል ቦርዱ የምርጫውን ውጤት ይፋ የሚያደርግበትን ቀን እንዲራዘም የተጠየቀውን ጥያቄ ለቦርዱ እንደሚያቀርቡና ቦርዱ እንደሚወስንበት ተናግረዋል፡፡

ቦርዱ ተገቢ ነው ብሎ ካመነበት ቀኑ ይራዘማል፡፡  እስከመቼ መራዘም እንዳለበት ቦርዱ ያስታውቃልበማለት አቶ ከማል ገልፀዋል፡፡

የቦርዱ ሊቀመንበር ጊዜያዊ የምርጫ ውጤት እንዳይገለፅ የሚለውን ሃሣብ ውድቅ አድርገዋል፡፡  ጊዜያዊ የምርጫ ውጤት መነገሩ ቦርዱ በግልፅነት እንደሚሰራ የሚያሳይና ሕዝቡን ለማስገንዘብ ይጠቅማል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ እስካሁን 200 በላይ በሚሆኑ የምርጫ ክልሎች ላይ አቤቱታዎች ቀርበውለታል፡፡

ለበለጠ መረጃ በእነዚህ ቁጥሮች ይደውሉ፡፡

የፕሬስ ኦፊሰር ጌታሁን አሞኘ   251 - 9 - 643738

ረዳት ፕሬስ ኦፊሰር ሕይወት አለማየሁ 251 - 9 - 487576

 
 
     
     
       
             
 
 
This site is designed by Afrolink Studio
Copyright © 2005 National Electoral Board of Ethiopia. All rights reserved.