የምርጫ ቦርድ የቅንጅት አባል ድርጅቶች ላደረጉት ውህደት
እውቅና አልሰጠም
ጥቅምት 17 ቀን 1997 ዓ.ም.
ቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ በአዲስ መልክ አደረኩ ያለውን ውህደት ሕጋዊ ዕውቅና በተመለከተ የመገናኛ ብዙሀንና ሌሎችም አካላት ማብራሪያ እንዲሰጣቸው ቦርዱን በተደጋጋሚ ጠይቀዋል፡፡ በዚህም መሠረት ቦርዱ የቅንጅቱን አመሠራረትና የአዲሱን ፓርቲ እውቅና በተመለከተ ማብራሪያ ለመስጠት ተገዷል፡፡
የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ አንድነት ፓርቲ - መድሕን (ኢዴአፓ-መድሕን)፣ የመላው ኢትየጵያውያን አንድነት ድርጅት (መኢአድ)፣ ቀስተደመና ኢትየጵያ ለዲሞክራሲና ማሕበረሰባዊ ፍትሕ ንቅናቄና የኢትዮጵያውያን ዲሞክራሲያዊ ሊግ (ኢዴሊ) ለግንቦት 7ቱ ምርጫ በአንድነት ለመንቀሳቀስ እንዲችሉ ቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ በሚል ስያሜ እወቅና እንዲሰጣቸው ጥቅምት 29 ቀን 1997 ዓ.ም. ለቦርዱ ባቀረቡት ማመልከቻና የመመስረቻ ሰነድ ጠይቀዋል፡፡ በመመስረቻ ሰነዱ አንቀጽ 9 በግልፅ እንደተመለከተው አራቱ ፓርቲዎች የፈጠሩት ቅንጅት ለንግቦት 7 ቀን 1997 ዓ.ም. የሕዝብ ተወካዮችና የክልል ምክር ቤቶች አባላት ምርጫ ጊዜ ብቻ የሚያገለግል ሆኖ የእያንዳንዱ ፓርቲ ሕጋዊ ሰውነት እንደተጠበቀ የሚቆይ ነው፡፡
በዚህም መሠረት የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ታህሣሥ 8 ቀን 1997 ዓ.ም. ለቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ የዕውቅና የምስክር ወረቀት ሰጥቷል፡፡ ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት የምርጫው ሂደት የቋጨ በመሆኑ ቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ የተሰጠው የዕወቅና ጊዜ አብቅቷል፡፡
ቦርዱ የቅንጅት አራቱ አባል ድርጅቶች በቅርቡ ውህደት ስለመፈፀማቸው እንደማንኛውም ሰው በመገናኛ ብዙሃን ከመስማት በስተቀር ለውህደቱ ሕጋዊ እውቅና ለማግኘት የቀረበለት ጥያቄም ሆነ የሰጠው የሕጋዊ ሰውነት ማጋገጫ የምስክር ወረቀት የለም፡፡ የተጠቀሱት ፓርቲዎች ውህደት ፈፅመው ከሆነ በሕጉ መሠረት ቀደም ሲል እያንዳንዳቸው የወሰዱትን የሕጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት በመመለስ ለአዲሱ ፓርቲ እውቅና ማመልከት ሲኖርባቸው ይህንን አላደጉም፡፡
ስለዚህም በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ የሚያውቃቸው ከላይ የተጠቀሱትን አራት የፖለቲካ ድርጅቶች በየራሳቸው ሕጋዊ ሰውነት መሆኑን እየገለፀ ከዚህ በኋላ ቦርዱ የሚኖረው ግንኙነትም ከነዚሁ አራት ፓርቲዎች ጋር ብቻ ይሆናል፡፡
የኢትዮጵያ
ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ
ጽሕፈት ቤት
ጥቅምት 17 ቀን 1997 ዓ.ም.
አዲስ አበባ፣
ለበለጠ መረጃ በእነዚህ ቁጥሮች ይደውሉ፡፡
የፕሬስ ኦፊሰር ጌታሁን አሞኘ 251 - 9 - 643738
ረዳት ፕሬስ ኦፊሰር ሕይወት አለማየሁ 251 - 9 - 487576 |