Top Banner
Site Map Links Contact Us
Home
Election Day Countdown
About NEBE
What's New
Electoral System
Legal Framework
Electoral Operations
Maps & Data
Domestic & International Observers
Election Results
Photo Gallery
 
መጋቢት 19 ቀን 1997 ዓ.ም.


የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ከመጪው ምርጫ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ የፕሬስ መግለጫ ሰጠ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ በመጪው ግንቦት 7 ቀን 1997 ዓ.ም. ለሚካሄደው የሕዝብ ተወካዮችና የክልል ምክር ቤቶች አባላት ምርጫ በቦርዱ እስካሁን የተከናወኑትንና እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን በተመለከተ ለሀገር ውስጥና ለውጭ ሀገር ጋዜጠኞች መግለጫ ሰጠ፡፡ በዕለቱም የቦርዱ ድረ-ገፅ እና አዲስ የተቋቋመው የፕሬስና ኢንፎርሜሽን ክፍል በይፋ ሥራቸውን ጀምረዋል፡፡

ቁጥራቸው አንድ መቶ የሚሆኑ ከ25 የአገር ውስጥና የውጭ የሚዲያ ተቋማት የተውጣጡ ጋዜጠኞችና ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት የፕሬስ ኮንፍረንስ በኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ በኩል የቦርዱ ሰብሳቢ አቶ ከማል በድሪ፣ የቦርዱ ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ተስፋዬ መንገሻና የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ ጽሕፈት ቤት ተጠባባቂ ኃላፊ አቶ መኮንን ወንድሙ ተገኝተዋል፡፡

በዚሁ ወቅት አቶ ከማል እንዳስታወቁት እስከአሁን የመራጮችና የዕጩዎች ምዝገባ በተሳካ መልኩ ተከናውኗል፡፡ የሶማሌ ክልልን ሳይጨምር በጠቅላላው ከ25.6 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ በመራጭነት መመዝገቡን ገልፀዋል፡፡

አቶ ከማል እንዳሉት በጠቅላላው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 1,845 ዕጩዎች የሚወዳደሩ ሲሆን 3,662 ዕጩዎች ደግሞ ለክልል ምክር ቤቶቸ ይወዳደራሉ፡፡ ከዚህ ውስጥ 423ቱ በግል የቀረቡ ሲሆን ቀሪዎቹ በ35 የፖለቲካ ፓርቲዎች የተወከሉ ናቸው፡፡

የቦርዱ ባለሥልጣናት እንዳብራሩት እስከአሁን በመራጮችና ዕጩዎች ምዝገባ ሂደት 50 የሚሆኑ ቅሬታዋች ቀርበው ከተመረመሩ በኋላ ውሣኔ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ በደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በሃድያ ዞን ሬርጌራ የምርጫ ክልል መራጮች ከአንድ በላይ ካርድ እንደተሰጣቸውና ዕድሜያቸው ለመምረጥ ያልደረሱ ሕፃናት ጭምር የመራጮች ካርድ በመሰጠቱ ምዝገባው እንዲሰረዝ መደረጉን አብራርተዋል፡፡

በዚሁ ሕገወጥ ድርጊት አንድ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ሕብረት አባል ተሳታፊ የነበረ መሆኑን ቦርዱ አረጋግጧል ያሉት የቦርዱ ኃላፊዎች ጉዳዩ በፖሊስ እየተጣራ መሆኑንና ጥፋተኞች ለፍርድ እንደሚቀርቡ ተናግረዋል፡፡

ከውጭ ሃገር ታዛቢዎች የአውሮፓ ሕብረት ልዑክ መምጣት መጀመሩንና የካርተር ማዕከልም ታዛቢዎቹን እንደሚልክ ማሣወቁ ተገልጿል፡፡ የአገር ውስጥ ታዛቢዎችን በተመለከተ ቦርዱ ፍቃድ ለመስጠት የሚያስችለው መስፈርቶችን እያወጣ እንደሚገኝ ተብራርቷል፡፡

የከፍተኛ ትምሕርት ተቋማት ተማሪዎችን በተመለከተ ተማሪዎቹ ባሉባቸው ተቋማት ሆነው ከየመጡባቸው የምርጫ ክልሎች ለሚወዳደሩ ዕጩዎች ድምፅ መስጠት የሚያስችላቸው ሥርዓት መዘርጋቱም ተጠቅሷል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የቦርዱን ገለልተኛነት፣ የፓርቲዎችን የምረጡኝ ዘመቻ ስነምግባርና እንዲሁም የቀድሞ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት በዕጩነት መመዝገብ አስመልክቶ ከጋዜጠኞች ለቀረቡ ጥያቄዎች መልስ ተሰጥቷል፡፡

 
 
 
 
   
   
 
 
This site is designed by Afrolink Studio
Copyright © 2005 National Electoral Board of Ethiopia. All rights reserved.